በምናውቀው ውስጥ

አንድ ወጣት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተመለሰና ግእዙን ንባቡን ማወቅ ፈለገ፡፡ ዳዊት ንባብ እንደ ጀመረ ገና አንዱን ምዕራፍ “ፍካሬን” እንዳጠና አንድ ተማሪ ያገኝና፡- “ተሜ አለቃ ገብረ ሃና ዳዊት ደግመዋል ወይ” ይለዋል፡፡ ተማሪውም ገርሞት፡- “አንድ ሰው ጳጳሱ ቄስ ናቸው ወይ ብሎ ጠየቀ፣ ሲመልሱለትም ያውም ተርፏቸው የሚናኙ አሉት፡፡ ያንተም ነገር እንዲህ ነው” አለው፡፡

አለቃ፣ አለቃ የተባሉት ብሉያትን ሐዲሳን፣ መነኮሳትንና ፍትሐ ነገሥትን በቃላቸው አውቀው ነው፡፡ ዳዊት መድገም ዛሬ የጀመረው ወጣት ራሱን ከአለቃ ጋር አነጻጸረ፡፡ ጳጳሱ ቄስ ናቸው ወይ ብሎ የጠየቀው አለባበሳቸው ለየት ብሎበት ይሆናል፡፡ ቅስና ግን የሚገኘው ከጳጳስ ነው፡፡ እንኳን ለራሳቸው ተርፏቸው የሚናኙ ናቸው፡፡ በመምህር እግር ሥር ተቀምጦ መማር የጠራ እውቀትን ያስገኛል፡፡ ትሕትናን ለመያዝ ይረዳል፡፡ መምህር ያላቸው ተማሪዎች እግር ከማጠብ ጀምሮ እጅ መንሣትን፣ አክብሮትን ይማራሉ፡፡ ይቀጣሉ፣ ይገሠጻሉ፡፡  መምህር የሌለው እውቀት የሙት ልጅ ነው፡፡ አሳዳጊ የለውም፡፡ እውቀት ትዕቢተኛ የማድረግ ጠባይ አለው /1ቆሮ. 8፡2/፡፡ ትዕቢትን የሚወልደው እውቀት ጅምር እውቀት ነው፡፡ ጎዶሎ ነገር መቦጫቦጩ አይቀርም፡፡ በምናውቀው ነገር ውስጥ ብዙ የማናውቀው ነገር አለና ብዙ ባወቅን ቁጥር ትሑታን እየሆንን እንመጣለን፡፡ የትልቅ ትሕትና መገለጫ ማጎንበስ ሳይሆን መማር ነው፡፡ አባቶች፡- “ትምህርትን መጥገብ የክህደት መንፈስ ነው” ይላሉ፡፡ በንቃት መስማት፣ መጻሕፍትን ማንበብ፣ መጠየቅ፣ ወደ ጉባኤያት መሄድ ትሕትና ነው፡፡ ቁመት የሚለካካ እውቀት ቁጥሩ ከድንቁርና ውስጥ ነው፡፡ ሶቅራጥስ፡- “ብዙ ባወቅሁ ቁጥር አለማወቄን ተረዳሁ” ያለው በዘመናት ሁሉ ሐቅ ሆኖ የሚኖር ነው፡፡

የሌሎች እምነት ተከታዮች መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ሲጀምሩ፡- “እናንተ መጽሐፍ ቅዱስን ትቀበላላችሁ” ይላሉ፡፡ የያዙት መጽሐፍ ቅዱስ ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተረጎመችውን መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ እውቀታችን ትሑታን እስኪያደርገን ድረስ እንወቅ፡፡ እውቀታችን ወደ ፍቅር እስኪያደርሰን ድረስ እንጸልይ፡፡ እውቀታችን የተግባር ሰው እስኪያደርገን ድረስ እንለማመድ፡፡ በምናውቀው ነገር ውስጥ የማናውቀው ብዙ ነገር አለ፡፡ ጌታ ሆይ ትሑታን አድርገን፡፡