ሥውር ዓይን

የመርሐ ግብሩ መሪ እኒያን ሊቅ ሲያስተዋውቅ፡- “በዓይነ ሥውር አቅማቸው ይህን ሁሉ ትምህርት ተምረው፣ ይህን ያህል ደቀ መዛሙርት አፍርተው…” እያለ በእርሱ አመለካከት ማድነቅ ያለውን ነገር አወረደው። ሊቁ ግን ሲነሡ፡- “ይህ ወንድሜ ያለውን ሰምቻለሁ። በዓይነ ሥውር አቅማቸው … ብሏል። ወንድሜ አምፑል ተቃጠለ ማለት መብራት ሄደ ማለት አይደለም…” ብለዋል። በርግጥም ሊቅ ናቸው። የላኛው ዓይን አምፑል ነው። አምፑል የሚሠራው በራሱ አይደለም፣ ዓይንም ያለ ልብ ከኃይል ምንጩ እንደ ተለያየ አምፑል ነው። ማስተዋል ከሌለ የላኛው ዓይን ከጌጥነት አያልፍም። እግዚአብሔር የሠራውን ለማድነቅ፣ የወደቁ ሰዎችን ለማንሣት፣ ወዳጆችን በፍቅር ለመመልከት… የሚያገለግለው የውስጥ ዓይን እንጂ የውጭ ዓይን አይደለም። ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው እያዩ የማያዩትን፣ እናያለን እያሉ የማያስተውሉትን፣ ሳያዩ እንመራለን የሚሉትን ለመውቀስ ነው። እግዚአብሔር የሚታየው፣ እውነት የሚገኘው በውስጥ ዓይን እንጂ በላይ ዓይን አይደለም። ወደ ተመስጦ ስንገባ፣ በሰቂለ ኅሊና ስንጸልይ፣ ቅኔ ስንቆጥር ምሥጢር ስናስስ፣ ሰዎችን ከልብ ስንሰማ ዓይናችንን እንጨፍናለን። የላኛው ዓይን ባካና ያደርጋል። ለኅሊና የቤት ሥራ እየያዘ ይመጣል። ከላይ የጠቀስናቸው አባት በሌላ ጊዜ፡-“ ዓይነ ሥውር ማለት የሳሎኑን መብራት አጥፍቶ የጓዳውን አብርቶ የተቀመጠ ነው” ብለዋል። በዚህ አገላለጥ መሠረት የሚንከባለል ዓይን ያለው አብዛኛው ሰው የጓዳውን አጥፍቶ የሳሎኑን አብርቶ የተቀመጠ ነው።

የቀደሙት አባቶች የቋንቋ እውቀታቸው ይደንቃል። ሲሰይሙ “ዓይነ ሥውር” ብለዋል። ሥውር ዓይን ያለው ማለት ነው። አንዱ የግልጽ አንዱ የውስጥ ዓይን ተደርጎለታል ማለት ነው። የላኛውን ዓይን ማጣት ሳይከለክላቸው ብዙ ታላላቅ ሥራ የሠሩ ሊቃውንትን ይህች ዓለም አስተናግዳለች። የላኛውን ብርሃን ማጣት ኃጢአት አይደለም፣ በውስጥ ጨለማ ተዝናንቶ መቀመጥ ግን ኃጢአት ነው። የላኛው በተአምራት ይወገዳል፣ የውስጥ ጨለማ ግን ያለ ትምህርትና እምነት አይወገድም።

ዓይን ተመልሳ ራሷን አይታ አታውቅም። ሌሎችን ታያለች ራሷን ግን አታይም። ሌሎች ያጎደሉትን ትገመግማለች፣ የራሷን ግን አታውቀዉም። የላኛዋ ዓይን ለሌሎች የሆነውን እያየች ቅንዓትን፣ የሌሎችን ሰላም እያየች ምቀኝነትን፣ የሌሎችን መውደቅ እያየች ፍርድን፣ የሌሎችን ርኩሰት እያየች ውድቀትን ይዛ ትመጣለች። በላይኛዋ ዓይን ብቻ መምራት አይቻልም። በላይኛዋ ዓይን ብቻ ማዘን አይቻልም። በላይኛው ዓይን ብቻ ማልቀስ አይቻልም።

በመንገድ ላይ እናቶቻችንን “እያዩኝ ሰላም ሳይሉኝ አለፉ” ስንላቸው የተለመደ መልስ ይሰጣሉ፡- “አይ ልጄ የሚያየው ልብ እንጂ ዓይን መሰለህ?” ይላሉ። ትልቁ ብርሃን ያለው ልብ ላይ ነው። የልብ ብርሃን ከጨለመ የላኛው አይቶ መርገጥ፣ አይቶ መጠንቀቅ፣ አይቶ ማዘን አይችልም።

ሥውር ዓይን ያስፈልገናል። ሥውር ዓይን ሲኖረን፡-

1-   ያለንን እናውቃለን። ስለጎደለን የምንጨነቀው ያለንን በትክክል ስላላወቅነው ነው።

2- እግዚአብሔር ዛሬም በሥራ ላይ መሆኑን እንገነዘባለን። ስለዚህ ተስፋችን ይታደሳል።

3- በአሁኑ ሁኔታ ሕይወትን አንመዝንም። አሁን ያለው ደግም ይሁን ክፉ እርሱ መጨረሻችን አይደለም። የሚመጣው የሚልቀው ነው።

4- ለጎዱን ሳይቀር በችግራቸው እንገኛለን።

5- በተገፉት ላይ አንጨክንም። ዓለም ተራ መሆኑ ይገባናል።

6- ለሌሎች ማካፈልን አንረሳም። ሌሎች እኛ ጋ ድርሻ አላቸው።

7- አንደበታችንን እንገዛለን። መልካሙን ቀን ለማየት አንደበትን መቆጣጠር ያስፈልጋልና። ጌታ ሥውር ዓይን ይፍጠርልን።