ሊቅነታችን

ሊቅነታችን

ሁለት ሆነው በመንገድ ሲሄዱ ይመሽባቸዋል፡፡ አንደኛው ይጠመጥምና አንደኛውን አስተዋዋቂ ያደርገዋል፡፡ ደህና ወደ ተባለ ቤት ቀረቡና አስተዋዋቂው፡- “ሰው አለ አገሩ አይከበር ሆኖ እንጂ በአገራቸው ትልቅ ሊቅ ናቸው” ሲል ቤት ለእግዚአብሔር ብለው አስገቧቸው፡፡ የተሻለ መኝታ ሊቅ ለተባሉት ተለቀቀላቸው፡፡ ሌሊቱ አለፈ፡፡ በትልልቅ ቤት የብራና ዳዊት አለ፡፡ አዋቂና የተከበረ ሰው ሲመጣ እንዲደግም ይጋበዛል፡፡ ያንን የብራና ዳዊት ለዚያ ሰው ሰጡት፡፡  እርሱም ተቀብሎ ንባቡን አያውቅ ገልጦ ማንበብ ያዘው፡፡ ለካ የያዘው ገልብጦ ነው፡፡ ቤተኞቹም ጨርሰው ይሆን ብለው ለማየትና ቁርስ ለማቅረብ ሲመጡ ዳዊቱን ገልብጠው እያነበቡ ነው፡፡ “አለቃ ዳዊቱ እኮ ተገልብጧል” አሏቸው፡፡ ያም ሰው ሊቅነት ባይኖረውም ብልጥ ነበርና፡- “አቃንቶማ ሁሉም ያነበዋል፡ የእኛ ሊቅነታችን ገልብጠን ማንበባችን ነው” አለ ይባላል፡፡

አዋቂ መባል ለጊዜው ያስከብራል፣ እውቀት የሚፈተን ነውና ቦታው ላይ ሲደርስ ግን ያሳፍራል፡፡ አዋቂ ከመባል አላውቅም ብሎ መማር የተሻለ ነው፡፡ አዋቂ መሆን ግን ያስደስታል፡፡ የተሻለውን ለመምረጥ ይረዳል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ያወቁና ያወቁ የሚመስሉ ወገኖች አሉ፡፡ ባልገባቸው ነገር አዎ አዎ የሚሉና ጭንቅላት የሚነቀንቁ አያሌ ናቸው፡፡ ትንሽ ማንበብ ሲጀምሩ ሰው ሁሉ መሃይም መስሎ የሚታያቸው አሉ፡፡ ማስቀደስ ሲጀምሩ ሊቁን “ቅዳሴ ይችላሉ ወይ?” ብለው የሚፈትኑ አያሌ ናቸው፡፡ በአገራችን ሁሉም ሊቅ ነው፡፡ እውቀት ግን የሚገኘው አላውቅም ብለን ትሑት ስንሆን ነው፡፡ ማወቅን ከጨረስን መኖርን ጨርሰናል ማለት ነው፡፡

ሁሉም አገር የራሱን ሊቅ ያከብራል፡፡ ይጠቀምበታል፡፡ የእኛ ደግሞ በተቃራኒው ነው፡፡ ሊቃችንን እናዋርዳለን፣ ስም እንሰጣለን፡፡ መንፈሳዊነት ቢጎድለን እንዴት ብልጥ መሆን አልቻልንም? እውነተኛ ሊቃውንትን ስንገፋ ዘቅዝቀው የሚያነቡትን ማስተናገዳችን ግድ ነው፡፡ ዛሬ ተሳዳቢዎችንና ቤተ ክርስቲያንን አዋራጆች ያተረፍነው ለዚህ ነው፡፡ ደረታቸውን ነፍተው መጽሐፉም ያለው “እርዱኝ እረዳችኋለሁ ነው” የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እንዲህ የሚል መጽሐፍ የለም፡፡ መጽሐፉ ያለው “ያለ እኔ አንዳች ማድረግ አትችሉም” ነው /ዮሐ. 15፡5/፡፡ መጽሐፉን ካላነበብን ያላለውን እናነባለን፡፡ ውስጣችን የሚሰማንን ያነበብነው ይመስለናል፡፡ ግሪኮች፡- “እስክንሞት ለዘላለም የምንማር ነን” ይላሉ፡፡ እስክንሞት የምንማር ከሆነ እስክንሞት የማናውቀው አዲስ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ የሚማር መንፈስ ያድለን፡፡

እኔ የክርስቶስ ባሪያ